ሕወሃት ወደ ደሴ ለመግባት ኃይሉን ለማጠናከር ከደላንታ እያጓጓዘው የነበረው ኃይል ሙሉ በሙሉ ተመታ | ቦሩ ስላሴ የነበረው የተሽከርካሪና የሰው ክምችት ወድሞበታል
አሸባሪውና ወራሪው የሕወሓት ኃይል በደሴ አቅራቢያ ያለው ኃይሉ እጅጉን በመመናመኑ ይህንን ኃይሉን ለማጠናከር ከደላንታ አካባቢ እያመጣው የነበረው ተጨማሪ ኃይል መንገድ ላይ እንዳለ በድሮን በተወሰደበት እርምጃ ሙሉ በሙሉ መደምሰሱ ተሰማ።
ሕወሓት በደላንታ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት እንደነበረው፤ በተለይም የደላንታ አንዳንድ አካባቢዎችን አለ ውጊያ መቆጣጠሩን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ከዚህ አካባቢ ያለው ኃይሉን በቀጥታ በደሴ አካባቢ እየወደመበት ያለውን ኃይል ለማጠናከር በ6 መኪና ሙሉ ታጣቂ ጭኖ መንገድ ላይ እንዳለ በድሮን ተመቶ ቀርቷል።
ሕወሓት በቦሩ ሜዳ አካባቢ የነበረው ኃይሉ መመታቱን በጠዋቱ 3 መረጃዎች የዘገብን ሲሆን ማምሻውን በደረሰን መረጃ መሰረት ደግሞ በቦሩ ስላሴ አካባቢ የነበረው የተሽከርካሪ እና የሰው ክምችቱ ሙሉ በሙሉ ተመቷል። አላሻ ሜዳ ላይ ያለው ኮምቦይም በተሳካ ሁኔታ በኢትዮጵያ ኃይሎች መመታቱን የሚገልጹት የዘ-ሐበሻ የመከላከያ ምንጮች በዚህ አካባቢ በሕወሓት ላይ እየደረሰ ያለው ኪሳራ እጅጉን የሚዘገንን ነው ተብሏል። ሕወሓት ደሴን እና ኮምቦልቻን ለመቆጣጠር የሕዝብ ማዕበል አሁንም እያጎረፈ መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች እስካሁን ይህ ሁሉ ኃይል እየወደመበትም ተስፋ ባለመቁረጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል በማመላለስ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ድሮኖችም አብዛኛዎቹን መንገድ ላይ እያስቀሯቸው ቢሆንም አንዳንዶቹን ግን ሸራ በማልበስ ልክ ሌላ ነገር እንደጫኑ በማስመል ታጣቂዎችን እንደሚያጓጉዙ ምንጩ ነግረውናል።