ኢትዮጵያን አስመልክቶ የኔዘርላንድ ፓርላማ ውይይት አካሄደ – አውሮፓ እና አሜሪካ ከማእቀብ ተቆጥበው በኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ላይ እንዲሰሩ አንድ የሆላንድ ፕሮፌሰር ገለጹ፣

(ዘሃበሻ) አውሮፓ እና አሜሪካ ከማእቀብ ተቆጥበው በኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ላይ እንዲሰሩ አንድ የሆላንድ ፕሮፌሰር ገለጹ፣
ፕሮፌሰሩ ይህንን የገለፁት የሆላንድ ፓርላማ ላይ ባደረጉት ውይይት ነው

ኢትዮጵያን አስመልክቶ የኔዘርላንድ ፓርላማ ውይይት አካሄደ


በኔዘርላንድ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኢትዮጵያን በተመለከተ ዛሬ ጠዋት ውይይት አካሄደ።የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገኙበት በዚህ ውይይት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና ግጭቱን በተመለከተ የተለያዩ የእርዳታ ስጪ ድርጅት ተወካዮች እና ፕሮፌሰር ያን አቢንክ ለአባላቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የኔዘርላንድ ቀይ መስቀል ተወካይ፣የሴቭ ዘቺልድረን እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት ወኪል እና በነጹህ የመጠት ውሃ አቅርቦት ላይ የሚሰራ ድርጅት ተወካዮች ስለግጨቱ እና እርዳታ አሰጣጡ ሂደት ገለጻ አድርገዋል።

በላይደን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ማዕከል ፕሮፌሰር የሆኑት ያን አቢንክ በበኩላቸው ግጭቱ በህወሃት መጀመሩን አስረድተው፣ነገር ግን እየተካሄደ ያለው( ) ሃሰተኛ ዘመቻ ነገሩን ሌላ መልክ እንዳሰጠው ገልጸዋል።

በመቀጠልም የአሜሪካ እና አውሮፓ መንግስታት ሁኔታውን በደንብ በመረዳት እንደ ማዕቀብ ካሉ እርምጃዎች በመቆጠብ ከኢትዮጵያ ጋር በዘላቂ እና ስትራቴጂካዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር እና ለግጭቱ መፍትሄ ለማምጣት ከመንግስት ጋር እንዲሰሩ ምክር ስጥተዋል። የአውሮፓም ሆነ ሌሎች የምዕራብ መንግስታት በህወሃት ደጋፊዎች እየተፍበረኩ የሚወጡ መረጃዎችን በጥንቃቄ በመመርመር ገንቢ ሚና እንዲጫዎቱ አሳስበዋል።

የክርስቲያን ህብረት ፓርቲ ተወካይ ጅምላ ግድያን እና የዘር ማጽዳትን በተመለከተ ላቀረበው ጥያቄ ፕሮፌሰሩ በሰጡት መልስ እየተሰራጨ ካለው ሃሰተኛ መረጃ አኳያ እንዲህ አይነት ሪፖርቶች በጥንቃቄ መመርመር እንዳለባቸው፣የኢትዮጵያ ስብዓዊ መንት ኮሚሽን አን የተመድ ስብዓዊ መብት ተቋም የማጣራት ሰራ ውጤት መጠበቅ እንደሚገባ ተባግረዋል።

የሴቭ ዘቺልድረን እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት ተወካይ ሚስስ አኪኒ ዋለንደር በበኩላቸውም በእነሱ በኩል የተባለውን ጅምላ ግድያ ስለመፈጸሙ ማርጋገጥ እንዳልቻሉ በመግለጽ ለፓርላማው ተወካዩች መልስ ሰጥተዋል።

ይህ በአንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ኮሚሽን በቅርቡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ተመሳሳይ ውይይት እንደሚያካሂድ እና የአሜሪካ መንግስት ጋር ተመሳሳይ የሆነ የቪዛ ክልከላ እና ሌሎች የማእቀብ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ለዘሃበሻ እየደረሱ ያሉ ዘገባዎች አረጋግጠዋል።