የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ሊጥል ነው ተባለ
(ዘ-ሐበሻ) በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ያቀረበው የኢትዮጵያ መንግስት አልቀበልም ብሏል በሚል ማዕቀብ ሊጥል መሆኑን የዘ-ሐበሻ የዲፕሎማቲክ ምንጮች አስታወቁ።
የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዘ-ሐበሻ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ላይ የሚጣለውን ማዕቀብ የአሜሪካ መንግስት ከአሁን ሰዓት በኋላ በማንኛውም ሰዓት ይፋ ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
የአሜሪካ መንግስት በድብቅ ባደረገው ስብሰባ ሁለት ዓይነት ማዕቀቦችን ለመጣል ሲነጋገር ቆይቷል። እነዚህም የማዕቀብ አይነቶች ታርጌትድ ማዕቀብ እና ኢኮኖሚክ ማዕቀብ የሚባሉ ነበሩ። ሆኖም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ታርጌትድ የሆነ ማዕቀብ እንደሚጥል ነው የዘ-ሐበሻ የዲፕሎማቲክ ምንጮች የሚገልጹት።
ታርጌትድ ማዕቀብ የሚያጠቃልለው የበረራ እቀባ አንዱ ነው። በዚህም መሰረት የተለያዩ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንዳይበሩ እቀባ ይወጣባቸዋል። እቀባ የሚወጣባቸው ባለስልጣናት ስም ዝርዝርን ዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ባያውቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና ሌሎችም እንድመኢኖሩበት ግን ከልምድ እንደሚታወቅ ገልጸዋል። እነዚህ በአሜሪካ መንግስት የበረራ እቀባ የሚወጣባቸው ባለስልጣናት ከበረራ እቀባ በተጨማሪ ያላቸው ሃብት ወይም ንብረት እንዳይቀሳቀስ ሊታገድም ይችላል። ይህ እቀባም ወደ አሜሪካ እንዳይበሩ ያላቸው ሃብትና ንብረት እንዳይነቀሳቀስ ከመታገዱ ውጪ ሌሎችም እርምጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ዲፕሎማሪቲክ ምንጮች ለዘ-ሐበሻ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ለመከላከያ ሰራዊቱ የጦር መሳሪያ ግዢ እቀባ አንዱ የታርጌትድ ማዕቀብ አንዱ አካል እንደሚሆን ምንጩ ተናግረዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ይህን ማዕቀብ ለመጣል የወሰነችው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የእርዳታ እንዳይዳረስ አድርጓል በሚል ገንዘብ እየተቀበሉ እነ ሲኤንኤን ባቀረቡት ሃሰተኛ ዘገባ ሲሆን በሁለተኛነት የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሓት የተኩስ አቁም አድርገው ድርድር እንዲቀመጡ ያቀረበውን ጥያቄ ኢትዮጵያ አልቀበልም ብላለች በሚል ነው። እንደ ዘ-ሐበሻ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ገለጻ አሜሪካ ይህን እንደምክንያትነት ታቅርብ እንጂ ምክንያቱ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ለአሜሪካ ፍላጎቶች አልታዘዝም በማለቱ፤ የሕዳሲው ግድብ ግንባታ እንዲሁም በተለይም ከኤርትራና ከሱማሊያ ጋር እየመሰረተ ያለው የኢኮኖሚ ጥምረት ለአሜሪካ ስጋት ስለሆነባት ነው።
“የጀርመን መንግሥት ዓለም አቀፍ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ባልደረባና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት አንቴ ዌበር ማክሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በቀጣናው ጉዳዮች ላይ በሰጡት አስተያየት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የአካባቢውን ትስስር ለማሳለጥ ከተቋቋመው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥት ተቋም ከሆነው ኢጋድ ውጪ በመንቀሳቀስ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ኤርትራን ያካተተ የሦስትዮሽ መንገድ መከተላቸው በሌሎች የቀጣናው አባል አገሮችም ሆነ በአካባቢው ላይ ጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ባላቸው አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ላይ ሥጋት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ለማምከን በተቻለው ዲፕሎማሲያዊ መንግድ በጋራ እየሠሩ መሆኑን፣ ከምንጊዜውም በላይ ምዕራባውያኑ በአካባቢው ፖለቲካ ላይ የተናበበ ጥምረት እንዲያደርጉ ማስገደዱን አክለዋል።” ሲል ሪፖርተር ዘግቧል።
የአሜሪካን ማዕቀብ መጣል ተከትሎም አውሮፓውያን እና ሌሎች ሃገራትም በኢትዮጵያ ላይ ይጥላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚገልጹት ምንጯ አሜሪካ ኢትዮጵያን እንደ አጋርነት ካጣች የምትጎዳው ራሷ አሜሪካ ናት ይላሉ።