ሽፍታው የሕወሓት የተራረፈ ቡድን ኮረም አካባቢ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ማስኮችን እና እህል የጫኑ መኪኖችን በእሳት አነደደ | ሹፌሮቹን ዘርፎ ረሽኗቸዋል
በተራ ሽፍታነት ተግባር ተሰማርቷል የሚባለው የተበታተነው የሕወሓት ኃይል ለትግራይ ሕዝብ እየሄደ የነበረን የኮቪድ 19 መከላከያ ማስኮችን፣ እና ሌሎች የ እርዳታ እህል የጫኑ መኪኖችን ኮረም አካባቢ ጨለማን ተገን አድርጎ በመዝረፍ እንዳቃጠላቸው ተገለጸ።
የሽፍታው ቡድን ትግራይ እና ሕዝቡ ከተረጋጋ እኔ እረሳለሁ በሚል ምክንያት ሕዝቡ እርዳታ እንዳያገኝ፤ እርዳታ የጫኑ መኪኖችን መንገድ ላይ ጠብቆ በመዝረፍ፣ ሹፌሮችን በመግደል፣ ንብረቶቹን በማቃጠል ተራ የሽፍታ ሥራ ላይ ተሰማርቷል ተብሏል።
የትግራይን መረጋጋት እና ወደ ሰላሟ መመለስ የማይፈልገው ይኸው የሽፍታ ኃይል በየቦታው በመደበቅ አልተባበርም ባለው ሕዝብ ላይም ጥቃት መሰንዘሩን ቀጥሏል። ቡድኑ ራሱ ገደሎ፣ ራሱ አቃጥሎ ቪድዮ እና ፎቶዎችን በማንሳት ኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች ይህን አደርጉ ብሎ ለሃሰት ፕሮፓጋንዳ እንደሚጠቀምባቸው ተገልጿል።
በቅርቡ የሰሜን ዕዝን እንዲመሩ የተሾሙት ሜ/ጀ ክንዱ ገዙ ጁንታው ሊከተለው ያሰበውን የፖለቲካ ሴራ ማጋለጣቸው የሚታወስ ነው።
“ከሀዲው ጁንታ በአንዳንድ የትግራይ የከተማ አካባቢዎች የተቀበሩ አስከሬኖችን ህብረተሰቡ አውጥቶ ቪዲዮ በመቅረጽ የተለመደ የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ለመስራት እና የዓለም ማህበረሰብን ለማሳሳት ለተከታዮቹ ትዕዛዝ አስተላልፏል ፡፡” ያሉት ሜጀር ጀነራል ክንዱ “በግጭት ወረዳ የሠራዊታን አባላትም ሆኑ የጁንታው ተከታዮች ሲሰዉ በክብር እንቀብራለን ፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን ባህል ነው ፡፡ ጁንታው ይህንን ስለሚያውቅ የማንም ይሁን አስከሬን ከተቀበረበት አውጥታችሁ አሰባስቡ ብሎ ትዕዛዝ አስተላልፏል ፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሽፍቶቹ አሁንም የሚያስቡት የፖለቲካ ትርፍን ነው ፡፡ ሙታን በሰላም እንዳያርፉ ከየአካባቢው እየተቆፈረ በማውጣት አዲስ ለሚመለምሉት ወጣት በመንግስት ላይ ጉዳት እንዳደረሱ በማሳየት ማነሳሻ ለማድረግ አስበዋል ፡፡” የሚሉት ሜ/ጀነራል ክንዱ “ሌላው በአጽሙ ዶክመንተሪ አዘጋጅተው ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በማሳየት የፌዴራል መንግስት ትግራይ ላይ ጭፍጨፋ ፈጸመ ለማስባል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ፡፡ የትግራይ ህዝብ ይህንን አረመኔያዊ ተግባር አይቀበለውም ፡፡ የትግራይ ህዝብ ሀይማኖቴ ፣ ባህሌም ሆነ ሞራሌ አይፈቅድልኝም ብሎ ይቃወመዋል ብለን እናምናለን ፡፡” ሲሉ ትናንት መናገራቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል በየቦታው የተበታተነውን የሽፍታ ቡድን ለመለቃቀም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች አሰሳ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል። ሽሬ አካባቢ ዛና የተባለው አካባቢ ፣ ነደር እንዲሁም አዴት የሚገኝ የተራረፈ የህወሓት ሽፍታ ቡድን ላይ እርምጃ መወሰዱን የመከላከያ ምንጮች ለዘ-ሐበሻ አስታውቀዋል።