አዜብ መስፍን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት በአዲስ አበባ ተሰጣት
የሃገሪቱ ባለስልጣናት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ መሪዎች ከሚያገኙት ጥቅማጥቅም መካከል አንዱ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ማግኘት ነው:: ይህ በህግ ከጸደቀ ዓመታት ቢሆኑትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ ዘመናዊ ለመሪዎች ብቻ ተሰርቶ የሚሰጥ ቤት እንደተሰጣት የዘ-ሐበሻ ምንጭ ገልጿል::
አዜብ መስፍን ከዚህ ቀደም ቦሌ ኖቭስ ሱፐር ማርኬት ገባ ብሎ በሚገኝ መንግስት በሰጣት ዘመናዊ የክራይ ቤቶች ቤት ውስጥ ትኖር የነበረ ሲሆን ይህን ቤት የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሙክታር ከድር ይኖርበት የነበረ ሲሆን አዜብ መለስ ከሞተ በኋላ ከቤተመንግስት አልወጣም በሚል እያመጸች ባለችበት ወቅት ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ሲፈለግ ሙክታር እንዲለቅ ተደርጎ እርሷ ከነቤተሰቧ ገብታበት ቆይታለች::
አሁን አዜብ በባሏ ምክንያት ከመንግስት ባገኘችው ጥቅም ይህን ቤት ለቃ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ተሰጥቷታል:: አሁን አዜብ ትኖርበት የነበረው የክራይ ቤቶች ቤትም ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዲገቡበት መደረጉን ዘ-ሐበሻ ሰምቷል::
አቶ ሽመልስ አብዲሳ አዲስ አበባ አቧሬ አካባቢ ይኖሩ የነበረ ሲሆን ከወራት በፊት አንድ ግለስብ ልጁን ለማሳከም ወደ ሽምለስ አብዲሳ መኖሮያ ቤት አጠገብ የሚገኝ ክሊኒክ በሚወስድበት ወቅት መኪናውን ሽመልስ አብዲሳ በር ላይ አቁመሃል በሚል ከጠባቂዎች ጋር በተነሳ ግብግብ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ዘ-ሐበሻ መዘገቡ አይዘነጋም:: የቀድሞው ሸመልስ ይኖርበት የነበረው አቧሬ አካባቢ የሚገኘው መኖሪያ ቤት መንገድ ዳር ከመሆኑም በላይ “መኪና ማቆም አይቻልም” የሚሉ ማስታወቂያዎች በግልጽ ስለማይታዩ የሽመልስ ጠባቂዎች እና መኪና አሽከርካሪዎች ሁልጊዜም ይወዛገቡ ነበር:: መንገደኞችም ይጉላሉ እንደነበር የአካባቢው ነዋርዎች ይናገራሉ::
አዜብ መስፍን በአሁኑ ወቅት ከቻይናውያን ባለሃብቶች ጋር በሽርክና በጨርቃጨርቅ ንግድ ሥራ ላይ መሰማራቷን ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም መዘገቡ የሚዘነጋ አይደለም::