የአለም ቤተክርስቲያናት ካውንስል(ደብሊው ሲሲ) ጊዜያዊ ዋና ፀሀፊ ዶክተር ዮአን ሱካ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የካውንስሉ አባል ለሆኑ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ቤተክርስቲያናት ደብዳቤ ፃፉ
የአለም ቤተክርስቲያናት ካውንስል(ደብሊው ሲሲ) ጊዜያዊ ዋና ፀሀፊ ዶክተር ዮአን ሱካ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የካውንስሉ አባል ለሆኑ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ቤተክርስቲያናት ደብዳቤ ፃፉ፡፡ በደብዳቤያቸው ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ግጭቶች፣ የጅምላ ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ስለመፈፀማቸው መስማታቸው እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትር በፃፉት ደብዳቤ ‹‹በትግራይ ክልል ውስጥ ሚሊዮኖች የረሀብ አደጋ ስጋት ውስጥ ስለመሆናቸው፣ ህፃናት ጠኔ ውስጥ ስለመውደቃቸውና አዲስ የበረሀ አንበጣ ወረራ ስጋት ስለመኖሩ እየተዘገበ ቢሆንም በግጭት ወደተጠቁት አካባቢዎች እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ጥቂት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ናቸው፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢዎች ከፍተኛ መፈናቀል የተከሰተ ከመሆኑም በላይ በሴቶችና ልጅ አገረዶች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ ነው፡፡ በክልሉ በአብዛኛው ቦታዎች የቴሌኮሚኒኬሽን ግንኙነት አሁንም ዝግ በመሆኑ ለተጎዱት ውጤታማ እርዳታ የመስጠት ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው እንገነዘባለን›› ብለዋል፡፡
ጨምረውም ‹‹መንግስትዎ ባለፉት ወራት በእነዚህ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ለሚገኙ ህዝቦች እርዳታ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት ብናውቅም ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶችም ለህዝቡ አስቸኳይ ምግብ፣ መድሀኒትና ሌሎች ድጋፎችን እንዲያቀርቡ ሊፈቅዱ ይገባል›› በማለት ገልፀዋል፡፡ ዋና ፀሀፊው ደብዳቤያቸውን በመቀጠል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይ በመተከል ብሄርን መሰረት ያደረገ የጅምላ ግድያና ጭፍጨፋ መከናወኑን እንደሰሙ አስታውቀው ይህን ተከትሎ ከአስር ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም አስረድተዋል፡፡
በትግራይና በቤኒሻንጉል ክልሎች በዚህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባለበት ወቅት ይህ አሳዛኝ ድርጊት መፈጸሙ ድርጅታቸውን እንዳሳሰበውም አስታውቀዋል፡፡ በደብዳቤያቸው መጨረሻም ‹‹በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ካጋጠማት ፈተና እንድትወጣ ለኢትዮጵያ እንፀልያለን፡፡ የተፈፀመውን አረመኔያዊ ድርጊትም እናወግዛለን፡፡ ግጭቱ፣ መፈናቀሉ፣ ክልላዊ ውጥረቱ እንዲሁም አጠቃላይ የአገሪቱ አለመረጋጋት እንዲቆምም እንፀልያለን›› ብለዋል፡፡