የችሎት ዜና
ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ምስክር እንዳይሰማ ሲል የእግድ ትዕዛዝ ሰጠ። ልደታ ፍ/ቤት ጥር 5/2013ዓ.ም. በዋለው ችሎት አቃቢ ሕግ ለዛሬ በባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ምስክሮችን ማሰማት እንዲጀመር መቅጠሩ ይታወሳል። ይሁን እንጅ ችሎቱ ምስክር መስማት አልቻለም። አቃቤ ሕግ ከጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ቸሎት ምስክር እንዳይሰማ ትዕዛዝ አምጥቻለሁ በማለቱ ምስክሮች ሳይቀርቡና ሳይደመጡ ቀርተዋል። ጉዳዬ በጠቅላይ ፍ/ቤት እስኪታይ ድረስ ችሎቱ ለየካቲት 16 ቀጠሮ ሰጥቷል። ዝርዝሩን እንደደረሰ እናቀርባለን! ጥር 2013ዓ.ም. አዘጋጅ፡ በወግደረስ ጤናው ፡፡
ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ ምርጫ ሳይሆን ሕዝበ ውሳኔ ነው የሚያስፈልጋት” (ስንታየሁ ቸኮል፤ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት፣የፖለቲካ እስረኛ)
ኦሕዴድ/ብልፅግና እኛን አዲስ አበባ ላይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳናደርግ እንደልማዱ ከልክሏል። በአንፃሩ የራሱን ካድሬዎች ፎቶ ግራፍ አሸክሞ በኦሮሚያ አሰልፏል። ስም እየተጠራ ጭምር የጦርነት ዘመቻ እየተከፈተብን ነው። በዚህ ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ ምርጫ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ቢደረግም እንኳን ታማኝነቱ አሳን ጭው ባለ ደረቅ ተራራ የማርባት ያህል ከባድ ነው። እነርሱ ‘አዲስ አበባ እምብርታችን ነች’ ይላሉ። ለእኛ ደግሞ ጉሮሯችን፤ እስትንፋሻችን ነች። ትግላችን የእምብርትና የጉሮሮ ጉዳይ ነው። ጉሮሯሯችንን ላለማዘጋት፤ እስትንፋሻችንን ላለማቋረጥ እስከ መጨረሻው እንታገላለን። በዚህ ትንቅንቅ ውስጥ ኦሕዴድ/ብልፅግና አሸናፊ ሆኖ ከተማዋን ለመሰልቀጥ ከሕገ ወጥ የመታወቂያ እደላው ጀምሮ የማይሠራው ግፍ የለም። በመሆኑም ፍትሐዊ ምርጫ ይደረጋል የሚል እምነት የለኝም።
ስለዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ ነፃነቱን፣ የሀገር ባለቤትነቱን ማረጋገጥ ያለበት በሕዝበ ውሳኔ (Referendom) ነው። በአስቸኳይ ሕዝበ ውሳኔ አድርጎ ራሰ ገዝ አድያም ሊሆን ይገባል። ይህም ሲባል ለአስሩ ‘ክልሎች’ የተሰጠው ፖለቲካዊ ሥልጣን ለአዲስ አበባም ሊሰጣት ይገባል። ይህ ሲሆን ኦሕዴድም ሆነ ሌላ የአንድ ብሔር ወኪል ፓርቲ በከተማዋ ጉዳይ ላይ ገብቶ ከሳሽም ፈራጅም ራሱ መሆኑን ያቆማል። የሕወሓት ልዩ ጥቅም ማዕከል የነበሩት ከአማራ የነጠቃቸው ራያና ወልቃይት ነበሩ። የኦሕዴድ ደግሞ አዲስ አበባ ሆናለች። አሁን ከልዩ ጥቅምም ታልፎ ከተማዋን የማጥፋ ተግባር ነው የተያዘው። ሆኖም እኛ ሳንፈርስ አዲስ አበባ አትፈርስም። አባቶቻችን በገነቧት ከተማ ፍርስራሽ ላይ አንቆምም። አዲስ አበባ የኦሕዴድ እስር ቤት አትሆንም። ሕዝብ ለራሱ ህልውና ሲል ሊታገላቸው ይገባል። ድል ለዴሞክራሲ!