በቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመራው የሕወሓት ጁንታ የዲፕሎማሲ ቡድን በየቀኑ ሃሰተኛ መረጃዎችን በትዊተር እያሰራጨ
በቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመራው የሕወሓት ጁንታ የዲፕሎማሲ ቡድን በየቀኑ ሃሰተኛ መረጃዎችን በትዊተር እያሰራጨ የዓለም ታላላቅ ተቋማትን እና ሃገራትን እያሳሳተ እንደሆነ እና ይህም የኢትዮጵያን መንግስት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው እንደሚገኝ አንድ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ምስጢራዊውን መረጃ ለዘ-ሐበሻ ተናገሩ::
ትናንት ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ከጀርመኗ መሪ አንጌላ ማርኬል ጋር ከተወያዩ በኋላ ወዲያውኑ በውጭ ላለው ዲያስፖራ “ዳሩ ግን፥ ዛሬም የጁንታው ሞት ያልተዋጠላቸው ከዥንጉርጉር ማህጸኗ የፈለቁ ሰዎች ከሀገራችን ጠላቶች ጋር እያበሩ፣ የተዛቡ መረጃዎች መርጨቱን የዕለት እንጀራቸው አድርገውታል። እንዳሻቸው መሆን ካልቻሉ ኢትዮጵያ እንድትኖር አይፈልጉም። በሕግ ማስከበር ዘመቻው ያጡትን ድል በወሬ ግንባር ለመመለስ ተንኮልን መሣሪያ፣ ሐሰትን ጥይት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።በመሆኑም በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፥ ስለ ሀገራችሁና ስለ ወቅታዊው ጉዳይ ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመናገር፤ የሀገራችንን መልካም ክብርና ስም ለማጥፋት የተነሱ ሰዎችን ድል በመንሳት፤ ሐሰትን በእውነት እንድታሸንፉ ጥሪ አቀርባለሁ።” በማለት አስቸኳይ ጥሪ ለማቅረብ የተገደዱትም የጀርመኗ መሪ የሕወሓት ጁንታን ለህግ ለማቅረብ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ዙሪያ የተዛባ አመለካከት ውስጥ መውደቃቸውን ተከትሎ ይመስላል ሲሉ እኚሁ ምንጭ ተናግረዋል::
ምንጩ እንዳሉት በውጭ ያሉ ዲፕሎማቶች በቁጥር አንድ ሁለት ተብለው ከሚጠቀሱት ውጭ በአብዛኛው በቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመራው የሕወሃት ጁንታ የዲፕሎማሲ ቡድን እየነዛ ያለውን ሃሰተኛ መረጃ ሊመክት ቀርቶ ምንም ዓይነት ሥራ እየሰራ አይደለም:: አብዛኛው የኢምባሲ ዲፕሎማት በኮቭድ 19 የተነሳ በያለበት ሃገር የመንግስትን ደሞዝ እየበላ ሥራ ከሚገባበት ቤቱ የሚቀመጥበት ቀን ይበዛል የሚሉት እኚሁ ምንጭ ቤቱ እንኳ ተቀምጦ ቢያንስ ትዊተር ከፍቶ ሃገሩን ሲከላከል አለመታየቱ እጅግ አሳዛኝና የሚያስቆጭ ነው ይላሉ::
አምባሳደርና ቆንስላ ጀነራል ተብለው የተመደቡት አብዛኞቹም በያሉበት ሃገር የጡረታ ጊዜያቸውን በንባብ የሚያሳልፉ ነው የሚመስሉት የሚሉት እኚሁ ዲፕሎማቲክ ምንጭ ምንም ዓይነት ሥራ እየሰሩ ባለመሆኑ አሁን ላይ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የዲፕሎማቲክ ጫናው በርትቷል:: ሕወሓቶች በኮቭድ 19 እና በኤች አይቭ የሞቱ ሰዎችን ፎቶ እና ስም በትዊተር እያሰራጩ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተገደሉ ንጹሃን በማስመሰል በትዊተር ያሰራጫሉ; በህወሓት ባለስልጣናት እና ወታደሮቻቸው የተደፈሩትን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ያላክካሉ; በተደራጀ መልኩ ሃሰተኛ መረጃዎችን ለውጭ ሚዲያዎች በመስጠት የኢትዮጵያን ስም ሲያጠፉ በየኢምባሲው የተሰገሰጉ ጡረተኛ ዲፕሎማቶች ግን የመንግስትና ሕዝብን ገንዘብ እየበሉ ዝምታን መምረጣቸውና እውነታውን አለማስረዳታቸው ጫናውን አብሶታል ይላሉ ምንጩ::
አንዳንድ የውጭ መንግስታት በእነቴዎድሮስ አድሃኖም ሃሰተኛ መረጃዎች ተሳስተው ከሕወሃት ጋር ጦርነቱ መቼም የሚያበቃ ባለመሆኑ ተደራደሩ የሚሉ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደሚያቀርቡ የገለጹት እኚሁ ዲፕሎማቲክ ምንጭ ጫናው ከ እለት ወደ እለት እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል:: በትግራይ ሕዝቡ በርካታ እርዳታዎችን እያገኘ ነው ሆኖም ግን አሁንም እነቴውድሮስ አድሃኖም የሚያሰራጩት መረጃ በተቃራኒው ነው:: በሌላ በኩል ከቤኒሻንጉል እና ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ ከ270 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እርዳታ እያገኙ ባይሆንም እንደነ ቴውድሮስ አድሃኖም የሚጮህላቸው ስለሌለ እነዚህ ከቤኒሻንጉል እና ከኦሮሚያ የተፈናቀሉት የውጭ እርዳታ ሰጪዎችንና መሪዎችን ትኩረት እንዳላገኙ ምንጩ ይናገራሉ::
ቴዎድሮስ አህዳኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ሥራው የተለያዩ ሃገራት መሪዎችና ድርጅቶች ጋር ስለሚገናኝ ስለሥራው ከተወያየ በኋላ የትግራይን ጉዳይ መረጃ አዛብቶ እያቀረበ ይገኛል:: የብልጽግና አመራሮች ይህን የዲፕሎማሲ ጫና በአንድ ላይ ከመቋቋም ይልቅ የውስጥ የስልጣን እና ለኔ ይገባኛል ሽኩቻ ውስጥ መወጠራቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዋጋ እያስከፈለው ነው ሲሉ ምንጩ አምርረው ለዘ-ሐበሻ ተናግረዋል::