ዋልድባ ገዳም አካባቢ የጀነራል ታደሰ ወረደ ጦር በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ተኩስ ከፍቶ ውጊያ ገጥሟል
እየተካሄደ ባለው የሕወሃት አመራሮችን እና የጦር መኮንኖችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ወይም የመደምሰስ ትግል የመጨረሻው ም ዕራፍ ላይ ይገኛል:: ጀነራል ታደሰ ወረደ, ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና ሌሎችም የሚገኙበት ይህ የሕወሓት 200 የሚሞላ ጦር በዋልድባ ገዳም አካባቢ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እጅ እንዲሰጡ በማይክራፎን በተደረገ ጥሪ ቢጠየቁም አሻፈረኝ በማለት ውጊያ መክፈቱን የዘ-ሐበሻ ምንጭ ገልጸዋል::
እየተዋጉ ሱዳን መግባትን ዓላማ ያደረጉት እነ ጀነራል ታደሰ ወረደ እና ጻድቃን ገብረትንሳኤ መንገዶች የተዘጋጉባቸው በመሆኑ እዚያው ዋልድባ ገዳም አካባቢ መታኮስ ጀምረዋል:: በየቦታው ተቆራርጠው የቀሩትን የሕወሓት ልዩ ኃይልና ሚኒሻ አባላትን በማስተባበር የትግራይን ገበሬ እህል እየዘረፉ ከቦታ ቦታ ሲሸሹ የከረሙት እነጀነራል ታደሰ ወረደን ከመግደል ይልቅ እጃቸውን ሰጥተው ፍርድ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቢፈልግም ይህ የሚሆን አይመስልም ይላሉ የመከላከያው ምንጭ:: እነ ጀነራል ታደሰ የመጨረሻቸው የሆነችውን ተኩስ እየተኮሱ ነው የሚሉት ምንጩ በመከላከያ ሰራዊቱ መደምሰሳቸው አይቀሬ ይመስላል ብለዋል::
እነጀነራል ታደሰ ወረደ ፍየል ውሃ ፣ ማይሃንሰ ፣ መጉዕ በረሃ ፣ ማይአርቃይ ተዳፋት ድልክ አካባቢ ፣ ማይአንበሳ ፣ ደደቢት ፣ አስገደ ፅምብላ ፣ ፀሊሞይ ፣ ፅልሙት ሩባ ( ጨለማ ወንዝ ) ፣ ማይጋባ እንዳባጉና መሻገሪያ ፣ አዲ ህርሚት ፣ ጠለምት በረሃው ፣ ዋልድባ ዋሻዎች አካባቢ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን በነዚህ አካባቢዎች ከትግራይ ገበሬዎች እህል ሲዘርፉ ቆይተዋል::
በሌላ በኩል የመከላከያው ምንጭ እንዳሉት በትግራይ ሴቶችን አስገድዶ እየደፈረ ያለው ራሱ ሕወሓት መሆኑን ተናግረዋል:: ከዚህ ቀደም ሕወሃቶች የኤርትራን መከላከያ ሰራዊት ዩኒፎርም በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እያሰሩ እንደነበር መጋለጡን ያስታወሱት እኒሁ ምንጭ ሕወሃት መቀሌን ለቆ ሲወጣ ከ እስር የለቀቃቸውን እስረኞች የኤርትራ ሰራዊት ዩኒፎርም በማስለበስ ሆን ተብሎ ሕዝቡ እንዲነሳሳ ይህን አሳፋሪ ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል::
በክልሉ በሚገኘው ኮማንድ ፖስት አብዛኛዎቹ እንደተያዙና የተያዙትም ይህን እንዳረጋገጡ የጠቀሱት ምንጩ “ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር የሚታወቁት ራሳቸው ሕወሓቶች ናቸው:: ከዚህ ቀደምም የመቀሌ ልጃገረዶች “ይሁኖ” ብለው ባለስልጣናት የሚፈጽሙት አስገድዶ መድፈር እንዲቆም ሰልፍ የወጡባቸው በነሱ ላይ ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ መከለከያ ሰራዊት እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ሥራ እንደማይሰራ ተናግረዋል::