የኢትዮጵያ መንግስት ሎቢ የሚያደርግ ድርጅት መቅጠሩ ተሰማ፡
ኢትዮጵያ የገጠማትን የዲፕሎማሲ ቀውስ ለመመከት በአሜሪካ ኮንግረስና በጆ ባይደን አስተዳደር ሎቢ የሚያደርግ ድርጅት መቅጠሯን ፍርይን ሎቢ ዘግቧል፡፡ እንደዘገባው የተቀጠረው ‹‹ቬናብል›› የሚባል በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ የህግ ተቋም ነው፡፡
በዋሽንግተን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከድርጅቱ ጋር በወር ሰላሳ አምስት ሺህ ዶላር ለመክፈል ስምምነት መፈፀሙም ተዘግቧል፡፡ በስምምነቱ መሰረት ውሉ ከፌብሩዋሪ አንድ ቀን ጀምሮ የሚፀና ሲሆን ለሶስት ወር የሚቆይ ነው፡፡ እንደአስፈላጊነቱ ውሉ ሊራዘም እንደሚችልም ዘገባው አስረድቷል፡፡
እንደዘገባው ቬናብል በአሜሪካ ፍትህ ቢሮ የመንግስት ግንኙነት ስራ ለመስራት ፈቃድ ያለው ሲሆን፣ በዋሽንግተን ለሚገኘው ኳታር ኤምባሲና ለሆንግ ኮንግ ንግድ ልማት ምክር ቤትም ወኪል ሆኖ እየሰራ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን የሎቢ ድርጅት ለመቅጠር የተገደደችው በተለይ በግብፅ በኩል ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ በመሆኑ የአፀፋ እርምጃ ለመውሰድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የግብፅ መንግስት በትራምፕ አስተዳደር ወቅት በዲፕሎማሲው ከፍተኛ የበላይነት ለመቀዳጀት ችሎ ከኢትዮጵያ እርዳታ ላይ እርዳታ እስከማስቀነስ ደርሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁንም ይህንን የዲፕሎማሲ ጦርነት ለመቀጠል አዲስ ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዘገባው አስረድቷል፡፡ የትራምፕን መሸነፍ ተከትሎ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ግብፅ ኤምባሲ በፍጥነት አዲስ የሎቢ ድርጅት መቅጠሩንም አስታውቋል፡፡ የግብፅ አዲሱ ሎቢ ድርጅት ‹‹ብራውንስቲን ሀያት ፋርበር ሽሪክ›› የሚባል ሲሆን የተፈራረመው ለአንድ አመት እንደሆነና ክፍያውም በወር ስልሳ አምስት ሺ ዶላር ነው ብሏል ዘገባው፡፡