የሕወሓቶቹ አባይ ጸሐዬ እና ዓለም ገብረዋህድ በወንበር ክፍፍል አለመግባባት ውስጥ ገቡ
በትግራይ በተካሄደው; ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ‘የጨረቃ” ባሉት ምርጫ ሕወሓት መቶ በመቶ ወንበሩን ማሸነፉን ተከትሎ ክልሉ አዲስ ባሻሻለው አዋጅ ቀሪዎቹን 20 በመቶ ወንበር በምርጫው ለተሳተፉ ተቃዋሚዎች ማከፋፈል የሚኖርበት ቢሆንም; የስብሰሃት ነጋን ቡድን የሚመራው ዓለም ገብረዋህድ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ ተወዳድረው ያሸነፉበት ምርጫ ጣቢያ በሌለበት ወንበር ይጋሩ መባሉን እንደማይቀበለው ለአባይ ጸሐዬ መናገሩና በዚህም ውዝግብ ውስጥ መገባታቸውን የዘ-ሐበሻ ምንጮች ገለጹ::
የትግራይ ክልል ምክር ቤት የጨረቃ የተባለው ምርጫ ከመካሄዱ ወራት በፊት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው በክልሉ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የምርጫ ሥርዓት ለውጥና በምክር ቤቱ ውስጥ ባለው የመቀመጫ ብዛት ላይ ጭማሪ ማድረጉ ይታወሳል:: ምክር ቤቱ በስብሰባው የክልሉን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48ን በማሻሻል ነው የምክር ቤቱ የመቀመጫ ቁጥር እንዲጨምርና እስካሁን የነበረውን የምርጫ ሥርዓት ያሻሻለው። በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት በክልሉ ከዚህ በፊት የነበረውን የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት በመቀየር በ”ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት” እንዲተካ በማድረግ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
በተጨማሪም በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ መቀመጫዎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ የአብላጫ ድምጽ ባገኘው የፖለቲካ ድርጅት የሚያዙ ሲሆን፣ 20 በመቶው ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና ለተወዳዳሪ ድርጅቶች እንደሚከፋፈል ይደነግጋል::
ሕወሓት ምርጫውን ሙሉ በሙሉ በማሸነፉ 80 ፐርሰንቱን ወንበር የሚወስድ ሲሆን ቀሪው ለተቃዋሚዎች መከፋፈል ይኖርበታል:: ይህን ተከትሎ ሕወሓትን ከኋላ ሆነው ከሚዘውሩት አዛውንቶቹ የሕወሓት አመራሮች መካከል አቶ አባይ ጸሐዬ “በክልላችን በተካሄድውምርጫ ህወሐት ሙሉ በሙሉ አሸንፏል:: ይህም ለትችት እየዳረገን ነው ስለዚህም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተወሰነ ድምፅ ያገኙ ካሉ በስምምነት ወደ ክልሉ ምክር ቤት የሚገቡበት ዘዴ ተፈጥሮ ቢገቡ ይሻላል የሚል አስተያየት” አቅርበው ነበር:: አባይ ለዚህ ያቀረቡት ምክንያቱም “ሙሉ በሙሉ ህወሐት ወንበሩን ተቆጣጥሮታል:: ይህም ሕዝቡን ምንም ለውጥ የለም እንዲልም ምክንያት ፈጥሮታል:: ለሰሚም ጥሩ አይሆንም::” የሚል ነበር:: አባይ አክለውም “ውሳኔው የህወሐት ስራ አስፈፃሚ የፖለቲካ ውሳኔ ቢሆንም የተቃዋሚዎቹ ነገር ቢታይላቸው ብትነጋገሩበት የሚል ሃሳብ ለዓለም ገ/ዋህድ ቢሰጥም አለም ዓልቀበልም የሚል አቋም ይዟል::
አለም በበኩሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ ተወዳድረው ያሸነፉበት ምርጫ ጣቢያ በሌለበት ወንበር ይጋሩ መባሉን እንደማይቀበለው ምክንያቱም ህዝቡ ይሆነኛል የሚለውን ፓርቲ መርጦ ሲያበቃ ድምፁ ታጥፎ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ወንበር ተቀንሶ ፖለቲካ ውሳኔ ይሰጥበት መባሉ አግባብነት እንደሌለው ለአባይ ጸሐዬ መልሶለታል:: ሕወሓት በተካሄደው ምርጫ 96.8 ፐርሰንት ህወሐት ያሸነፈ ሲሆን፣ ባይቶና 44 ሺ ድምፅ በትግራይ ደረጃ ማግኘቱን፣ ውድብ ነፃነት ትግራይ 30 ሺ በትግራይ ደረጃ ድምፅ ማግኘቱን፣ ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ 11 ሺ በትግራይ ደረጃ ድምፅ ማግኘቱን እንዲሁም አሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 1000 ብቻ ከጠቅላላ ምርጫ ማግኘቱን የታወቀ መሆኑን ከዚህ በመነሳት ወንበር እናካፍላቸው የሚል ሀሳብ እንደማይቀበለውና ምናልባት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የሚከራከረው አካል ከመጣ የህዝብ ድምፅ ሸውደው ወንበር እናካፍላቸው የሚሉ ሰዎች የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ ለማሳመን እንደሚከራከራቸው ገልፆለታል:: ሲል ምንጩ ተናግሯል::
በዚህም ውዝግብ ውስጥ ናቸው የሚለው ምንጩ በሕወሓት ውስጥም ወንበር እንስጥ አንስጥ በሚል ውዝግብ መፈጠሩን ገልጾልናል::
–