የዘሀበሻ የእለቱ 5 አጫጭር ዜናዎች!

 

የዘሀበሻ የእለቱ 5 አጫጭር ዜናዎች!

1

ካልቪን ክሌይንና ቶሚ ሂልፊገር የተሰኙትን ታዋቂ የልብስ ብራንዶች የሚያመርተው ፒቪኤች ኮርፖሬሽን ከመጪው ሰኞ አንስቶ ከኢትዮጵያ ምርት መቀበል እንደሚያቆም አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ላለፉት አምስት አመታት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ፋብሪካ የነበረው ሲሆን ይህንን ፋብሪካ ሰኞ እንደሚዘጋውም ገልጿል፡፡ በፋብሪካው ውስጥ ያለውን ንብረት ቀደም ብሎ ለአንድ ኢትዮጵያዊ የስራ አጋሩ መሸጡን ያስታወቀው ፒቪኤች ይህንን እርምጃ የወሰደውም በአገሪቱ ውስጥ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ‹‹በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ለሁሉም ሰራተኞቻችን የሶስት ወር ደመወዝን ጨምሮ ሁሉንም ካሳ እንከፍላለን፡፡›› ብሏል፡፡ ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ፋብሪካውን የከፈተው በአጎዋ የቀረጥ ነፃ እድል ለመጠቀም ሲሆን ይህ እድል ከመጪው ጃንዋሪ ወር አንስቶ እንዲቋረጥ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትእዛዝ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡ (ጀስት ስታይል)

2

የአርመን ዲያስፖራ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛረህ ሲናንያን በኢትዮጵያ ያሉ አርመናዊያን ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ገለፁ፡፡ ኮሚሽነሩ ከአርመን ኒውስ ጋር ዛሬ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ አርመናዊያን በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሲሆን በጣም ብዙ አመት በዚያ የቆዩ ናቸው፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ታጣቂዎች ወደአዲስ አበባ እየተቃረቡ ነው የሚለውን መስማታችን እጅግ አሳስቦናል፡፡ ምክንያቱም ምን እንደሚፈጠር አናውቅም›› ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙት የአርመን አምባሳደር ጋር የቅርብ ግንኙነት በማድረግ ላይ እንዳሉ ያስታወቁት ኮሚሽነሩ ጨምረውም ‹‹እኛ አርመናዊያን ያለውን ሁኔታ እየተከታተልነው እንገኛለን፡፡ ዜጎቻችን የእኛን እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜ ያንን የማድረግ የሞራል ግዴታ አለብን›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

3

የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች በኢትዮጵያ ውስጥ ታስረው የነበሩ ስድስት የድርጅቱ ሰራተኞች መለቀቃቸውን ገለፁ፡፡ በተጨማሪም ሰባ የተመድ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ከእስር መፈታታቸውን ያስታወቁት ቃል አቀባዩ አሁን አምስት የተመድ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎቹ የታሰሩት በሰመራ እርዳታ የጫኑ መኪናዎችን እያሽከረከሩ ወደትግራይ ሊሄዱ ሲሉ እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡ 

4

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ባደረጉትን ንግግር አሜሪካ(የባይደን አስተዳደር) በአፍሪካ ላይ ያለውን ፖሊሲ ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ ንግግራቸው የአፍሪካ መሪዎች ከኢትዮጵያና ከሱዳን ቀውስ ልምድ ወስደው የህዝብን የመልካም አስተዳደርና የለውጥ ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጡበት አሳስበዋል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ፅንፈኝነት፣ አምባገነንነትና ሙስና መስፋፋቱ ዲሞክራሲንና ሰብአዊ መብትን እየተፈታተነው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ አሜሪካ ሁሉንም የአፍሪካ አገራት እኩል አጋር አድርጋ እንደምትቆጥር የጠቀሱት ብሊንከን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአሜሪካ አፍሪካ ጉባኤ ለማድረግ ማቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡

5

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር ክልል ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንደሆነ አስታወቀ፡፡ ባለስልጣኑ የአየር ክልሉ ከስጋት ነፃ እንደሆነና በኢትዮጵያ አየር ክልል ላይ በደህንነት ለመብረር እንደሚቻል ገልጿል፡፡ ባለስልጣኑ ይህንን መግለጫ ዛሬ ያወጣው ትላንት የአሜሪካ በፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ነው፡፡ የአቪየሽን አስተዳደሩ ባወጣው ማስጠንቀቂያ ወደአዲስ አበባ የሚገቡ አውሮፕላኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመሬት ወደአየር ለሚተኮሱ ጦር መሳሪያዎች ሊጋለጡ እንደሚችሉ በመጥቀስ ፓይለቶችን አስጠንቅቆ ነበር፡፡ በማስጠንቀቂያው ህወሀት እስከ ሀያ አምስት ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ሮኬት፣ ሚሳኤል ወይንም ሌላ ፀረ ታንክና ፀረ አውሮፕላን ጦር መሳሪያ ሊተኩስ እንደሚችል ገልፆ ይህንን ማስጠንቀቂያ ያወጣው ግን በሲቪል አቪየሽኑ ላይ ዛቻ ስለቀረበ እንዳልሆነ አስረድቷል፡፡