ኤኤፍፒ ከእስራኤል መንግስት ጋር በኢትዮጵያዊያን የተነሳ ውዝግብ ውስጥ ገባ
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት የሆነው ኤኤፍፒ ከእስራኤል መንግስት ጋር ውዝግብ ውስጥ ገባ፡፡ ለዚህ ውዝግብ መነሻ የሆነው እሁድ እለት በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ አስመልክቶ ያቀረበው ዘገባ ነው፡፡
ቤተ እስራኤላዊያኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዘመዶቻቸው ካለው የፀጥታ ስጋት አንፃር በአስቸኳይ ወደእስራኤል እንዲጓዙ የሚጠይቅ ሰልፍ ማከናወናቸው ይታወቃል፡፡ ኤኤፍፒ ይህንን ዘገባ ካቀረበ በኋላ ‹‹የእስራኤል መንግስት ወደ ሰማኒያ ሺህ ያህል ኢትዮጵያዊያንን ወደእስራኤል ቢወስድም አብዛኛዎቹን እያኖራቸው ያለው በአወዛጋቢው ዌስት ባንክ ነው›› ብሎ ነበር፡፡ ይህ አባባሉ ግን የእስራኤል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን እንዳስቆጣ ተዘግቧል፡፡ የእስራኤል ማእከላዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ መረጃ ላይ የተቀመጠው ከጠቅላላው በእስራኤል የሚኖር የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በዌስት ባንክ የሚኖረው ከሁለት ፐርሰንት ያነሰ ብቻ መሆኑን የቢሮው ሀላፊ ታማር ስቲርንታል ገልፀው የዜና አውታሩ ዘገባውን እንዲያርም ጠይቀዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ኤኤፍ ፒ ዘገባውን እንዳላስተካከለው ታውቋል፡፡ ኤኤፍፒ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ይህንኑ ዜና ተርጉሞ ሲያቀርብ ተመሳሳይ ስህተት አለማካተቱ ጉዳዩን በአንክሮ እንዲመለከቱት እንዳደረጋቸው የቢሮ ሀላፊዋ ጨምረው መግለፃቸውን ከቢሮው ቡለቲን ላይ አንብበናል፡፡