በወረኢሉ ግንባር ከአየር ጥቃት የተረፉ ከ1000 በላይ የሕወሓት ታጣቂዎች እጅ ሰጡ
(ዘ-ሐበሻ) ሕወሓት በትናንትናው ዕለት ወረኢሉን ተቆጣጥሬያለሁ በሚል ሰበር ዜና ያስነገረው በድሮን ድብደባ ከደረሰበት በኋላ መሆኑን የመከላከያው ምንጭ ለዘ-ሐበሻ ገለጹ። ወደ ጎጃም እሄዳለሁ ብሎ መንገድ ጀምሮ ከመካነሰላም ጀምሮ እየተጠረገ የመጣው የሕወሓት ኃይል ከአቃስታም ሲመታ ወደ ደቡብ ወሎ ወረኢሉ መሸሹን ትናንት መዘገባችን ይታወቃል። ትናንት ከወረኢሉ ከነበረ ተጨማሪ የሕወሓት ኃይል ጋር ተቀላቅሎ ውጊያ ቢከፍትም በድሮን በተወሰደ ድብደባ በርካታ አባላቶቹ ሙት እና ቁስለኛ ሆነውበታል።
ይህ ኃይል በድሮን ድብደባው እንዲዛባ ከተደረገ በኋላ መከላከያው ወዲያኑ ገብቶ በመክበብ ከ1000 በላይ የሚሆኑትን መማረኩን የመከላከያው ምንጭ ተናግረዋል። እንደምንጩ ገለጻ ሌላው በዚህ አካባቢ የነበረውና ከባድ መሳሪያዎችን ጭኖ ተመልሶ ወደ አቃስታ መስመር የሄደው የሕወሓት ኃይል ቦምባ ተራራ አካባቢ ውጊያ መጀመሩን ገልጸው ወደ አቃስታ መድፍ እየተኮሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የሕወሓት ኃይል በወረኢሉ መስመር በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአቃስታ መስመር ደግሞ ከጎጃም በመጡ ሚኒሻዎችና የደቡብ ወሎ ገበሬዎች በሁለቱም አቅጣጫ እንዳይሄድ ስለተዘጋበት ያለው አማራጭ በቦምባ ተራራ ላይ ውጊያውን መቀጠልና በዚያው አካባቢ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ በመሆኑ አሁን መድፎችን እየተኮሰ ቢሆንም ይህንን ኃይል ለመጨበጥ የሰዓታት ጉዳይ ነው የሚፈጀው ሲሉ ምንጩ ለዘ-ሐበሻ ነግረዋል።
መከላከያው በወረኢሉ ግንባር የተማረኩትን በቴሌቭዥን በቶሎ ሊያሳይ እንደሚገባውም እኚሁ የመከላከያው ምንጭ ተናግረዋል። መከላከያው እያገኘው ያለው ድል በአግባቡና በቶሎ አለመዘገቡ ብዙ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑንም አክለዋል።