(ዘ-ሐበሻ) “በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ አንደኛ ጠላት ሱዳን ነች። ድንበራችንን ዘልቆ በመግባት መሬት መቆጣጠሩና ንጹሃንን እየገደለ መዝረፉ ሳያንስ፤ በአንድ በኩል የሕወሓትና ቅማንት ታጣቂዎችን፣ በሌላ በኩል የጉሙዝ ታጣቂዎችን አሰልጥና፣ ከለላ ሰጥታ እየላከች ኢትዮጵያን ሰላሟን ለመንሳት ተግታ እየሰራች ነው” ይላሉ የዘ-ሐበሻው የመከላከያ ምንጭ መረጃ ማቀበሉን ሲጀምሩ። “የኢትዮጵያ መንግስት ስጋቱ የሆነውን የሱዳን መንግስት ከአንድ ሳምንት በፊት እንዳደረገው መደበኛ ባልሆነ ጦርነት አንድ ቀበሌ እንዳስለቀቀው ሳይሆን በይፋ ሱዳን ጦርነት እንደከፈተችብን ቆጥሮ ይፋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመር አለበት” ሲሉ አስተያየታቸውን ያክላሉ።
የሱዳን ጦር አዛዦች ሳይቀር የተሳተፉበት፤ ሁለት የሕወሓት ታጣቂ ኮለኔሎች ያካተተው 320 የሚሆን የሕወሓት ታጣቂዎችን አሰልጥኖ በሁመራ በኩል የገባው ሃይል በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አይቀጡ ቅጣት ቢቀጣም፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ከመተማ እስከ ጭልጋ የሕወሓትና ቅማንት ታጣቂዎችን አስገብቶ ሽብር ሊፈጥር ቢሞክርምና ቢደመሰስበትም የሱዳን መንግስት አሁንም አላረፈም የሚሉት የዘ-ሀበሻ ምንጭ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ 500 የሚሆኑ የጉሙዝ ታጣቂዎችን ልኳል። የሕዳሴውን ግድብ የሚጠብቀውና በድንበር ያለው መከላከያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከሱዳን የመጡት እነዚህ የጉሙዝ ታጣቂዎች በመከላከያው ላይ ተኩስ ቢከፍትም በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን የዘ-ሐበሻው ምንጭ አረጋግጠዋል።
ከሱዳን ሲመጡ ከተደመሰሱት ታጣቂዎች በተጨማሪ በሃገር ውስጥ ጫካ ውስጥ ተደብቀው ከነበሩ ታጣቂዎች መካከል እጃቸውን የሰጡትና ወደ ሰላም ለመመለስ ለሚፈልጉት ወደ ተሃድሶ ማዕከል ገብተው ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነም ተሰምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በሀገራዊ ጉዳዮች እና በቀጠና ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረና ከክልል አመራሮች ጋር የሚካሄድ የሁለት ቀናት ስብሰባ ትንናት መጀመሩን መግለጻቸው ይታወቃል። ዛሬ የሚጠናቀቀው ስብሰባም መንግሥት በቀጣይ ሦስት ወራት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አስመልክቶ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሏል። የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንዳሉት የስብሰባው ዋና አጀንዳም ሱዳን እየፈጸመች ያለው ጥቃትና የደቀነችው ብሔራዊ ስጋት ነው።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ – የህዳሴ ግድባችን ሕልውናችንና የሕዝባችን አንጡራ ሃብት በመሆኑ በግድቡ ላይ የሚቃጡ ትንኮሳዎችና ጥቃቶችን ለመከላከል የምዕራብ ዕዝ ከመቼውም ጊዜ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉ የዕዙ ም/አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀው ግብረ – ኃይል ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ብ/ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ገልጸዋል።
የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ ሠራዊቱ ዝግጁነቱን አረጋግጦ ይገኛልም ብለዋል።
ጄኔራል መኮንኑ አክለውም ፣ የውሃ ሙሌቱን ማንም የውጪ ኃይል አያስቆመውም፤ የሰራተኞቹ ደኀንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ይጠበቃል፤ ስራው ያለምንም እንቅፋት እንዲከናወንም በየደረጃው ያለ የሰራዊት አባል ከሌሎች ተጓዳኝ የጦር ክፍሎች ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን በማለት ተናግረዋል።