Site icon www.zehabeshanews.com

የአማራ ክልል በየቦታው ተወጥሯል – ክልሉ የመንግስት ሥራ ሊያቆም ይችላል

የአማራ ክልል በየቦታው ተወጥሯል –

ክልሉ በበጀት እጥረት የመንግስት ሥራ ሊያቆም ይችላል –

በአዊ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በጭልጋ – በዋግ ህምራ ዞን በታጠቁ በሕወሓት የሚደገፉ ኃይሎች ጥቃት ተሰንዝሮበታል 

(ዘ-ሐበሻ) የአማራ ክልል በበጀት እጥረት የተነሳ የመንግስት ሥራ ሊያቆም እንደሚችል እየተነገረ ባለበት በዚህ ሰዓት ክልሉን በሕወሓት የሚደገፉ ታጣቂዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለማፍረስ ወጥረውት ውጊያ ከፍተውበታል። 

ከሕወሓት ጋር የተደረገው ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ በኋአ የአማራ ክልል ለክልሉ የያዘውን በጀት ለወልቃይት እና ራያ አካባቢዎች በማዋሉ የተነሳ ገና ስድስት ወር ሳይሞላው የክልሉ በጀት እየተገባደደ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ከቀጠለም ክልሉ የመንግስት ሥራ መስራት ሊያቆም እንደሚችል እየተነገረ ነው።

ሕወሓት የወልቃይት እና የራያን በጀት አውድሞ ጦርነት ከፍቶ ተሸንፎ ከተባረረ በኋላ የመንግስት እና ህዝባዊ ሥራ እንዲጀመር ያስደረገው የአማራ ክልል የራሱን በጀት በመጠቀም ቢሆንም የወልቃይት እና የራያን ጉዳይ ከሚደግፉ ዲያስፖራዎች እንኳ የበጀት እርዳታ ጠይቆ የሚሰጠው ማጣቱን የሚገልጹት ምንጮች አሁን የፌዴራል መንግስቱ ድጋፍ ካላደረገለት፤ ለሰራተኛ የሚከፍለው ባለመኖሩ፣ ክልሉ የመንግስት ሥራዎችን ሊዘጋ እንደሚችል የዘ-ሐበሻ ምንጮች ገልጸዋል። በተለይም በራያና በወልቃይት ጉዳይ ሲታገሉ የቆዩ ወገኖች የክልሉን መንግስት በተለያየ መንገድ እንዲያግዙም ድጋሚ ጥሪ ሊቀርብ እንደሚችል ተነግሯል።

በሕወሓት የሚደገፉ የአማራ ክልልን ለማጥፋት የሚሰሩ ኃይሎች በአሁኑ ሰዓት  ክልሉ በዚህ የበጀት ችግር ባለበት ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት ከፍተውበታል። በሰሜን ሸዋና በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን ያለበት አካባቢ ዋና ትኩረት ያገኘ ቢሆንም በሌሎችም አካባቢዎች የአማራ ክልል በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቃ እንደሚገኝ ነው ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።

በሕወሓት የሚደገፈውና ከሱዳን ሰልጥኖ የመጣው የቅማንት ኃይል ነኝ የሚለው ተላላኪ ቡድን በጎንደር ጭልጋ የአማራ ልዩ ሃይል ካምፕ ላይ እና በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተደብቀው ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን እነርሱን ለመደምሰስ በአሁኑ ወት ልዩ ኃይሉም መከላከያውም ትግሉን እንደቀጥሉ ነው።

በሌላ በኩል በሕወሓት የሚደገፈው የጉምዝ ታጣቂ የሽፍታ ቡድን ወደ አማራ ክልል አገው አዊ ዞን በመግባት በትናንትናው ዕለት ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሮ ነበር።  በአማራ ክልል የአዊ ዞን እንዳስታወቀው “ታጥቆ የመጣውን የሽፍታ ቡድን በመደምሰስ ጠላት   የውርደት ማቅ ማልበስ ተችሏል” ሲል ገልጿል።

“በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓንጓ ወረዳ አዲስ አለም ቀበሌ በቀን ሚያዝያ 12/08/2013 ዓ.ም  ከቀኑ 4፡00 ስዓት አከባቢ  የተደራጅ ሽፍቶች ወደ አከባቢው በመግባት ማህበረስብ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሊያደርሱ ሲሉ በአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሽና በአከባቢው ማህበረሰብ አፀፋዊ ምላሽ በመስጠት ከጠላት ሀይል 4 በመደምሰስ ጠላት ያሰበውን ሴራ በማክሸፍ ወደ መጡበት መመለስ  ተችሏል፡፡” ሲል ገልጿል።

የሕወሓት  ሽፍታ ቡድን ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ዋግ ህምራ ዞን በመግባት የአካባቢውን ሚኒሻዎች ገድሎ መድሃኒት ቤቶችንና ሌሎች መጋዘኖች ዘርፎ መሄዱን መዘገባችን የሚታወቅ ሲሆን በአካባቢው አሁንም ከፍተኛ ውጥረት ሰፍኗል።

የአማራ ክልል በአሁኑ ሰዓት በየአቅጣጫው ተወጥሯል የሚሉት የዘ-ሐበሻ ምንጭ የገጠመው ከባድ ፈተና ነው ብለውታል።

Exit mobile version