–
በሰሜን ሸዋ በተለይም በአጣዬ ፣ በካራቆሬ፣ በሸዋሮቢት፣ ማጀቴ፣ አላላ፣ አንጾኪያ እና አካባቢዎች ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ እንዳለፉት 3 ቀናት የተኩስ ድምጽ ባይሰማም ታጣቂው ኃይል ራሱን ለሌላ ጥቃት እያዘጋጀ ሊሆን ስለሚችል ሕዝብ በጥንቃቄ ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ ” የሰሜን ሸዋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት የገጠመንን ወረራና ጥቃት በተረጋጋና በተቀናጀ መንገድ መመከት ላይ እናትኩር! ሲል ጥሪ አቀረበ | ከደረሰው ጉዳት ባልተናነሰም የጥፋት ሀይሎች ይበልጥ ህዝቡን በማሸበር የባሰ ስነ ልቦናዊ ጉዳት እየሰነዘሩበት ይገኛሉም ብሏል
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ልዩ ኃይል ከአካባቢው ሚሊሻ ጋር በመተባበር በአጣዬ ፣ በካራቆሬ፣ በሸዋሮቢት፣ ማጀቴ፣ አላላ፣ አንጾኪያ እና አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረውን የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ለማጽዳት እየሰሩ መሆኑን ተከትሎ በነዚህ አካባቢዎች ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የተኩስ ድምጾች እንዳለፉት 3 ቀናት የማይሰማ ቢሆንም፤ ምናልባት ታጣቂው ኃይል ራሱን ለሌላ ዙር ዘር ፍጅት እያዘጋጀ ሊሆን ስለሚችል ሕዝቡ በንቃት ራሱን እንዲከላከል እና እንዲጠብቅ ጥሪ ቀርቦለታል።
በአጣዬ ከተማ ባለፈው ረቡዕ እለት አንድ መኖሪያ ቤት መቃጠሉን መነሻ በማድረግ በተፈጸሙ ጥቃቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ቤት ንብረታቸው ወድሞ፣ ቤተክርስቲያን ተቃጥሎ፣ የተሰደዱ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም እያሻቀበ መሆኑ ተገልጿል።
ሰላማዊ ሰዎች ግን ዛሬም ከአጣዬ ፣ከካራቆሬ፣ ከቆሪሜዳ፣ ከጀብውሃና ከሸዋሮቢት ከጥቃቱ ሸሽተው በየጫካው በመሆን የድረሱልን ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ሚያዚያ 8 ቀን 2013 ከካራቆሬ ተፈናቅለው ሰለሎ በሚባል አካባቢ በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ከሁለት ሺህ በላይ ዜጎች መንግስት ካለ እንዲሁም የሰው ልጅ ጉዳይ የሚገዳቸው ሁሉ እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ሰብአዊ እርዳታ እና የደህንነት ጥበቃ በእጅጉ ከሚያስፈልጋቸው መካከልም ከሸዋሮቢት ከተማ ሚያዚያ 9 ቀን 2013 ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በተፈፀመባቸው ጥቃት እንዲሁም በስጋት ሸሽተው አርማኒያ በምትባል የገጠር ከተማ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ የሚገልሱት ተፈናቃዮች በተለይ ህጻናት የሚበሉት እንኳ እንዳጡ፤ ሴቶች ራሳቸውን መጠበቂያ እንኳን እንደሌላቸውና ማንም እርዳታ ይዞ እንዳልደረሰላቸው ገልጸዋል
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት የገጠመንን ወረራና ጥቃት በተረጋጋና በተቀናጀ መንገድ መመከት ላይ እናትኩር! ሲል ጥሪ አቀረበ።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ “በቅድሚያ በሰሞኑ በዞናችን ማህበረሰብ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ውድ ህይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን ሞት የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን።” ብሏል።
“በአጣዬ ከተማ የተጀመረው ጥቃት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ተስፋፍቶ የሰው ህይወት መጥፋትና መቁሰል እንዲሁም መፈናቀልንና የንብረት ውድመትን አስከትሏል። በማህበረሰባችን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚሰነዝረው የኦነግ ሸኔ ጥቃትን ለመመከት መላው መዋቅራችን ከፀጥታ አካላት ጋር ሆኖ በመስራት ላይም ይገኛል።የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን ለማገዝ፣የቆሰሉትን ለማሳከምም ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን አሁን ላይ ችግሩን ለመመከት የምንሰራውን ሥራ በትብብርና በመረጋጋት እንድንፈፅመው እንጠይቃለን።” የሚለው የሰሜን ሸዋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት “ከደረሰው ጉዳት ባልተናነሰም የጥፋት ሀይሎች ይበልጥ ህዝቡን በማሸበር የባሰ ስነ ልቦናዊ ጉዳት እየሰነዘሩበት ይገኛሉ።” ሲል ገልጾታል። “በሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዎችን በአካልና በተለያዩ የፅንፈኛ ማህበራዊ ገፆች ስነ ልቦናውን የማዳከም ጫና በማድረግ በተግባር ግን የጠላት ሀይል ሳይገባ ለዘረፋ የተንቀሳቀሱ ጥቂት የኛው የጥፋት ተሰላፊ ኃይሎች መኖራቸው ጉዳዩን ይበልጥ በብልሃት ማየትን ይጠይቃል።
ትግሉ ህይወት የማትረፍና ጠላትን የመመከት እንደመሆኑ መጠን በወሬ በመሸበር ሳይሆን ተደራጅቶ በመስራት መሻገር ያስፈልጋል።ይህን የለየለት የአማራ ጠልና ሀገር አፍራሽ ሀይል የሚገባውን እርምጃ ወስዶ በማረምም ረገድ የፌደራልና የክልሉ መንግስት አሁንም ዘለቄታዊ መፍትሔ በሚገኝበት ሁኔታ ላይ እንዲያግዝ በድጋሚ እንጠይቃለን። ሲል ባወጣው መግለጫ ላይ ጥሪውን አቅርቧል።