Site icon www.zehabeshanews.com

የሕወሓት ትራፊዎች በፈጸሙት ጥቃት የተነሳ በመላው ትግራይ ኤሌክትሪክ ተቋረጠ | የቴሌኮም አገልግሎትም የለም

የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ “- በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ፀረ ማጥቃት የምንመለስበት ሁኔታ : ትግራይ በተሟላ አስተማማኝ በተባለ ደረጃ ነፃ አውጥተን ቀጣይ ፓለቲካዊ እጣ ፈንታ ለመውሰድ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር በሚያስችለን ደረጃ ዝግጅታችን አጠናክረናል::” ሲሉ መግለጻቸውን ተከትሎ ሕወሓት ሊፈጽማቸው ያቀዳቸው እቅዶች መካከል አንዱ ዛሬ መክሸፉ ተሰማ።

ዛሬ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ወልዲያ ባለ ጉሙሩክ ኬላ በተደረገ ፍተሻ 23 ካርቶን ፈንጅ ተይዟል። 1 ካርቶን  ውስጥ 9  ፈንጅ የያዘ  ነው ያለው የዘ-ሀበሻ ምንጭ ሹፌሩ ኮምቦልቻ በፖሊስ ቁጥጥር እንደሚገኝ ገልጿል።

ይህ ከሕወሓት በድብቅ ወደ ከተማ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረው ፈንጂ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ሊፈጽመው ያሰበውን ሽብር ያጋለጠ ነው ሲሉ ምንጮቹ ይናገራሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የጁንታው ትራፊዎችና በየቦታው ተቆራርጠው የቀሩ ታታቂዎቹ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በፈፀሙት ጥቃት በመላው ትግራይ ኤሌክትሪክ ዳግም መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ፡፡

የጁንታው ርዝራዦች አዲጉዶም በተባለ አካባቢ ከአላማጣ – መሆኒ – መቐለ በተዘረጋው ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ባደረሱት ጥቃት ነው በክልሉ ኤሌክትሪክ የተቋረጠው፡፡

ከዚህ ቀደም መስመሩ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበረና ለመጠገንም ረዘም ያለ ጊዜ እንደወሰደ ይታወሳል፡፡

ክልሉ ኃይል ከሚያገኝባቸው መስመሮች አንዱ የአላማጣ – መሆኒ – መቐለ መስመር ሲሆን የተከዜ አክሱም መስመር ደግሞ  የጥገና ሥራው እየተከናወነ እንደነበር መገለፁ አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የወደመውን መሰረተ ልማት ዳግም በመጠገን መልሶ ኃይል ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ ቴሌ ጂነረተሮቹ ካልሰሩ በስትቀር የቴሌኮም አገልግሎትም ሊቋረጥ እንደሚችል ምንጮች ይናገራሉ።

ጌታቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ – ስለዚህ በምናደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ይሁን የህዝቡ ሁኔታ የወገን ሁኔታ እያጠናን : አሁን ከተሞች የማስለቀቅ ጉዳይ ውስጥ የምንቻኮልበት ምክንያት የለም:: ከተሞቻችን የራሳችን ናቸው የትም አይሄዱም : ከተሞቻችን የጠላት አውድማ እንዳይሆኑ የሚቻለንን እናደርጋለን:: 

– መሬቶቻችን ማንም አጉሯ ዘለል ገብቼ ይዥያለው ስላለ : ይዝዋቸው እንደማይቀጥል እናውቃለን:: በቅርቡ በደንብ ማየት ትጀምራላችሁ:: በዚህ ደረጃ መሰራትን ያለበት ስራ እየሰራን ነው : እየሰራን እንቀጥላለን::

– ሰራዊታችን በየጊዜው ያሉበትን ድክመቶች እየገመገመ : ስልጠናዎች እያካሄደ ጠንካራ የተሟላ ቁመና ላይ ለመድረስ አሁንም የሚያስፈልጉን ነገሮች አሉ:: ምክንያቱም ጦርነቱ መሬት ለማስለቀቅ ብቻ ሊሆን አይችልም:: በዋናነት እነዚህን አስቸጋሪ ጣቶች የሚያንቀሳቅሱ ጭንቅላቶች መቆረጥ አለባቸው:: 

Exit mobile version