የመንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፦ ያለፈው ጥቅምት በተጀመረውና መንግሥት «የሕግ ማስከበር» ባለው ዘመቻ ወቅት በንፁሃን ዜጎች ለደረሰው ማንኛውም ጉዳት የኢትዮጵያ መንግስት ማዘኑን አስታውቋል።
መንግስት አያይዞም በዘመቻው ወቅት በአንድ ሰላማዊ ሰው ላይ የሚደርሰው ሞት እንኳ አሳዛኝ መሆኑን ገልፆ ሆኖም ዘመቻው በጥንቃቄ የተካሄደ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች አልተጎዱም ማለቱን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ያሳያል።
በክልሉ የንፁሃን ዜጎችን ሞት በተመለከተ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጨው ዘገባም «ከእውነት የራቀና በመረጃ ያልተደገፈ» ነው ብሏል። የሞቱ ሰላማዊ ዜጎች ምን ያህል እንደሆኑ ግን ቁጥራቸውን ከመግለፅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያው ተቆጥቧል።