የአለም የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን በሱዳን፣ በኢትዮጵያና በጅቡቲ የሚገኙ ማህበራት በአስቸኳይ የሀያ ሰባት ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
እንደመግለጫው እነዚህ ሶስት አገራት ባለፉት አስራ ስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ሶስት መቶ ሀምሳ አምስት ሺህ፣ ሱዳን ሶስት መቶ ሺህ እንዲሁም ጅቡቲ አምስት ሺህ በተለያየ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን በቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበራቸው በኩል እየረዱ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ እነዚህ ማህበራት ይህንን እርዳታቸውን ለመቀጠል ይረዳቸው ዘንድ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ፌዴሬሽኑ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ ጨምሮ እንደገለፀው ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሶስት መቶ ሀምሳ ሺህ የስዊዝ ፍራንክ፣ ለሱን አራት መቶ ዘጠና ስምንት ሺህ እንዲሁም ለጅቡቲ ሀምሳ ሺህ ፍራንክ ቢመድብም የሚያስፈልገው ግን ሀያ ሰባት ሚሊዮን ነው፡፡