ከጅጅጋ እስከ ባህርዳር፤ ከአፋር እስከ ወለጋ፤ ከጎንደር እስከ ቀብሪዳር፤ ከጋምቤላ እስከ ቤኒሻንጉል፤ ከደብረማርቆስ እስከ ሐረር በመለስ ዜናዊ ስም የተሰየሙ ፓርኮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ወዘተ ስማቸው ላለፉት 3 ዓመታት እየተፋቀ በሌላ ሲቀየሩ ቢቆይም በአዲስ አበባ በመለስ ዜናዊ ስም ያሉ ነገሮች ሳይነኩ ቆይተዋል።
አሁን ግን ጊዜው እየደረሰ ይመስላል። በአዲስ አበባ በመልስ ዜናዊ አካዳሚ የተሰራው ሕንጻ ለ እናቶች እና ህጻናት ልዩ ዘመናዊ ሆስፒታል እንዲሆን ተወስኗል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህንጻውን ዲዛይኑን በማሻሻል ወደ ሆስፑታነት እንዲቀየር እያስደረገ ይሆን ይህም በአጭር ቀናት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የዘ-ሐበሻ ምንጮች ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች በመለስ ዜናዊ አካዳሚና መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ስም የተመዘገቡና ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ይገኛሉ። እነዚህን ቦታዎች ምን ለማድረግ እንደታሰበ ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ የለም።
ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሕወሓት ነባር ታጋይና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ናቸው። ቀዳማዊ እመቤት በነበሩበት ወቅት የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ማኅበር (ትዕምት ወይም ኤፈርት) መሪ ነበሩ። ወ/ሮ አዜብ፤ የባለቤታቸው መታሰቢያ የሆነው የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢም ናቸው። በአሁኑ ሰዓት አዜብ መስፍን ከመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ስራ በላይ በጨርቃጨርቅ ንግዱ ላይ እንደበረቱበት ነው ለዘ-ሐበሻ የሚደርሱ መረጃዎች የሚያመላክቱት።
አንዳንድ ምንጮችም የመለስ ዜናዊ አስከሬን ከለውጡ በኋላ ከአዲስ አበባ ስላሴ ቤተክርስቲያን ተወስዶ በትግራይ ስለመቀበሩ ሲናገሩ ቆይተዋል።