በመድረክ ስሟ ቤቲ ጂ ተብላ የምትጠራው ድምጻዊ ብሩክታዊት ጌታሁን በቅርቡ ልትሞሸር መሆኑን እጩ ሙሽሮቹን ያነጋገረው የዘሃበሻ ባልደረባ አረጋግጧል። ቤቲ ጂን ለትዳር ያጫት በሎስ አንጀለስ ከተማ የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት የሆነው ኤልያስ ወንድሙ ነው።
ኤልያስ ወንድሙ ባለፈው ሳምንት በሎስ አንጀለስ ከተማ ለቤቲ የቃልኪዳን ቀለበት አድርጎላታል። ዛሬ ቅዳሜ ደግሞ እነ አርቲስት ደበበ እሸቱ የሚገኙበት ሽማግሌዎች ወደ ቤቲ ቤተሰብ ለጥያቄ መሄዳቸው ታውቋል።
ድምጻዊት ቤቲ ጂ የመላው አፍሪካ የሙዚቃ ሽልማት (AFRIMA) በሦስት ዘርፎች በማሸነፍ ከዘመኑ ምርጥ ድምፃውያን አንዷ መሆንዋን አስመስክራለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዐህመድ የሰላም ኖቤል በተሸለሙበት በኦስሎ የNobel መድረክ ላይ ተገኝታ በድንቅ ስራዎችዋ አለምን ያስደመመች፣ በCoke Studio ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈች፣ ከሃገርኛ ቋንቋዎች ውጪ በኢንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ የማዜም ችሎታ ያለት ድምጻዊ ናት። ከጥበብ ስራዋ ጎን ለጎን በበጎ አድራጎት ስራዎች እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የበጎ ፈቃድ አምባሳደ ሆና ታገለግላለች።
የጸሃይ አሳታሚ ባለቤት የሆነው ኤልያስ ወንድሙ ወደ አሜሪካ ከመሄዱ በፊት በተለያዩ የህትመት ስራዎች አሻራውን ያኖረ ሲሆን አሜሪካ እንደገባ የ “ኢትዮጵያን ሪቪው” መጽሄት አዘጋጅ ሆኖ ለአመታት አገልግሏል። ጸሃይ አሳታሚን ካቋቋመ በኋላ ከ150 በላይ ለትምህርት እና የጥናት ማመሳከርያ የሚሆኑ መፅሐፍትን ለሕትመት አብቅቷል። አኤልያስ ላበረከተው አስተዋዓኦ ከተለያዩ ተቋማት ሽልማቶች ተበርክተውለታል።
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት የዳግማዊ አጼ ምኒልክን ከፍተኛ መኮንን ሜዳይ ለኤልያስ ሲሸልመው ብርቱ ጥረቱን በመገንዘብ ነበር። የሎስ አንጀለሱ ሎዮላ ማሪሙንት ዩኒቨርሲቲም የ 2018 Hidden Heroes Recognition Award አበርክቶለታል።
በጋዜጠኝነት እና በአሳታሚነት ለአመታት የሰራው ኤልያስ ወንድሙ ፔን ኢንተርናሽናል በተሰኘው አለም አቀፉ የፕሬስ ተሟጋች ተቋም ውስጥም የቦርድ አባል በመሆን አገልግሏል። በዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋም ውስት እያገለገለ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ፈተናዎች በአለም መድረክ እንዲታዩ ብዙ ጥሯል። በተለይ ደግሞ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ እና ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በፕሬሱ ለከፈሉት መስዋዕትነት አለም አቀፍ ሽልማት እንዲያገኙ አድርጓል።
ኤልያስ ወንድሙ ከለውጡ በኋላ ደግሞ “የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ” ቦርድ አባል እንዲሆን በጠቅላይ ሚንስትሩ ተሹሞ እያገለገለ ይገኛል። ፀሃይ አሳታሚ በአሁን ሰዓት በአንድነት ፓርክ ውስጥ መጽሃፍ ኬዎስክ ከፍቶ እያገለገለ ነው።