Site icon www.zehabeshanews.com

“በአሜሪካ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን መራጮች በቨርጂኒያ ምርጫ ለባይደን መልእክት አስተላልፈዋል” – ዘ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ

(ዘ-ሐበሻ ዜና) ዘ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ‹‹በአሜሪካ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን መራጮች በቨርጂኒያ ምርጫ ለባይደን መልእክት አስተላልፈዋል›› ሲል ዘግቧል፡፡ ጋዜጣው በቨርጂኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መራጮች ለምን ለዩንግኪን ድምፃቸውን ሊሰጡ ቻሉ? ይህስ እንዴት በሌሎች ቦታዎች ለዲሞክራቶች ችግር ሊፈጥር ይችላል? በማለት ሰፊ ትንታኔ አስነብቧል፡፡ በትንታኔው ግርማ መኮንን የተባለውን ኢትዮጵያዊ ጠቅሶ ይህ ሰው ራሱን የዲሞክራቶች ታማኝ ደጋፊ አድርጎ ይቆጥር እንደነበር አውስቷል፡፡

በሰሜናዊ ቨርጂኒያ መኖር በጀመረባቸው ሁለት አስርት አመታትም የዲሞክራቲክ ተመራጮችን በገንዘብ ከመደገፍ አንስቶ በስልክና ቤት ለቤት እየሄደ ቅስቀሳ ያደርግላቸው እንደነበር አስረድቷል፡፡ እንደዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ዘንድሮ ግን ግርማ የመረጠው ሪፐብሊካኑን የሀምሳ ሁለት አመት እጩ ግሌን ዩንግኪንን ነው፡፡ ለምን ይህን እንዳደረገ ለጋዜጣው ሲናገር ‹‹በባይደን አስተዳደር ያለው ዲሞክራቲክ ፓርቲ በያዘው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እኛን ገፍቶናል፡፡ እኛ ዲሞክራቶችን የምንደግፈው በሲስተማቸው እምነት ስለነበረን ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባል አሁን ቸል የተባለ ያህል የህመም ስሜት ውስጥ ገብቷል›› ብሏል፡፡

ጋዜጣው እንደግርማ ሁሉ ሌሎች የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላትም ያለፈው ወር ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ በያዙት አቋም የተነሳ እውቅና ለመንፈግ ሰፊ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ህወሀትን በመደረፍ እያደረገ ያለውን ጥረትና ጫና እንዲያቆም ጥሪ ሲያቀርቡ የቆዩት ኢትዮጵያዊያን ከኋይት ሀውስ ተገቢ ምላሽ ባለማግኘታቸው ይህንን መልእክታቸውን በምርጫ ካርዳቸው ለማስተላለፍ መፈለጋቸውንም አስረድቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ባለው ጊዜ ዲሞክራቶች በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጠንካራ ድጋፍ የነበረው መሆኑን ጋዜጣው ጨምሮ አውስቷል፡፡

የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበሩ አቶ መስፍን ተገኑ ለጋዜጣው በሰጡት መግለጫም ‹‹መንግስት የያዘው አካሄድ አግባብነት የሌለው በመሆኑ በዲሞክራት ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በሚያደርስበት በዚህ አካባቢ ላይ ቁጣችንን አሳይተንበታል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ዘመቻ ወቅት ሪፐብሊካኑ እንዲመረጡ ቅስቀሳዎችን ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናትና ሬስቱራንቶች እንዲሁም በስልክ ሜሴጅ በስፋት ሲያከናውኑ እንደነበርም ገልፀዋል፡፡ ይህም ወደሰላሳ ሺ ያህል ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት ቨርጂኒያ ዲሞክራቶች የነበራቸውን የበላይነት ለሪፐብሊካን እንዲያስረክቡ ማድረጉን ጋዜጣው አስታውቋል፡፡

በርት ባዩ የተባለ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ለዋሽንግተን ፖስት በሰጠው መግለጫ ይህ አይነቱ ስራ በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች በሚከናወኑ ምርጫዎችም እንደሚቀጥል አስረድቷል፡፡ ሲናገርም ‹‹ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ እንደተካዱ ተሰምቷቸዋል፡፡ በተለይ ግን ይህ ስሜት ያደረባቸው በዲሞክራት ፓርቲው ላይ ነው›› ብሏል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ የሚኖሩ ከመሆኑ አኳያ በምርጫ ላይ ውሳኔ ሰጪ የመሆናቸው እድል እየተስፋፋ እንደሚመጣ ጋዜጣው ጨምሮ አስረድቷል፡፡

Exit mobile version