(ዘ-ሐበሻ ዜና)አንድ ቢሊዮን ብር የሚያወጣውን የብሄራዊ ቤተ መንግስት እድሳት ፕሮጀክት ለማስጀመር የኮንትራክተሮች ምርጫ ከጫፍ እየደረሰ መሆኑን ዘ ሪፖርተር እንግሊዘኛ ጋዜጣ ዛሬ ዘግቧል፡፡ በሀይለስላሴ የተሰራውን ይህንን ቤተመንግስት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እቅድ መቀረፁ ይታወቃል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኒኤል ማክሮን የዛሬ ሁለት አመት ተኩል ገደማ ቤተመንግስቱን በጎበኙበት ወቅት ይህንን እቅድ በፋይናንስ ለመደገፍ ቃል መግባታቸውም ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ሀያ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ወይንም አሁን ባለው ምንዛሬ አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ ለእድሳት ፕሮጀክቱ መድቧል፡፡
ፕሮጀክቱን ለማከናወን በወጣው ጨረታ መሰረት ከአስር በላይ ተጫራቾች መወዳደራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ተጫራቾችን የመምረጥ ሂደት እየተከናወነ እንደሚገኝ ያስረዳው ዘገባው እድሳቱ ሲጠናቀቅ ቤተመንግስቱ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆንም ገልጿል፡፡