(ዘ-ሐበሻ ዜና) የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በባይደን አስተዳደር ወደኋይት ሀውስ የተጠሩ መጀመሪያው የአፍሪካ ፕሬዝደንት መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ ሰሞኑን የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በኬንያ መመላለስ ማብዛታቸው የሚታወቅ ሲሆን በመጪው ሰኞ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም ናይሮቢ ይገባሉ፡፡ አሜሪካ ከኬንያ ጋር እንዲህ አይነት የቅርብ ትስስር የፈጠረችው ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኘ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ምእራባዊያን በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ለውጥ ለመፍጠር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማዘዣ ጣቢያቸውን ያደረጉት ናይሮቢን ነው፡፡
ይህንን እቅዳቸውን ለማሳካትም መቀመጫውን በናይሮቢ ያደረገ ‹‹ሲቱ ኤፍሲ›› የተሰኘ ግብረ ሀይል አቋቁመው ያለፈውን አንድ አመት በንቃት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ግብረ ሀይሉ በሚዲያዎች ሀሰተኛ ዜናዎችን ከማስለቀቅ አንስቶ በተመድ ውስጥ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ እስከመክፈትና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እስከመፍጠር ድረስ ባለ በሌለ አቅሙ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን አሁን የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡
የዚህ ግብረ ሀይል ህልውና ከህወሀት ህልውና ጋር በቀጥታ የሚያያዝ መሆኑ መገለፁ አይዘነጋም፡፡ ዋነኛ አላማው ህወሀት ተመልሶ ስልጣን እንዲይዝና ኢትዮጵያን በሰላማዊ መንገድ እንደዩጎዝላቪያ እንድትገነጣጠል ማድረግና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተመሳሳይ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሆነም ከዚህ ቀደም በስፋት ተዘግቧል፡፡ በዚህ ግብረ ሀይል ውስጥ የኬንያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትም ይገኙበታል፡፡ በዚህ ሴራ የተጠለፉት የኬንያ ባለስልጣናት በተሰጣቸው ግዳጅ መሰረት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማጋነንና የአፍሪካ ቀንድ ስጋት አድርገው በመግለፅ ስራ ውስጥ ተጠምደውም ቆይተዋል፡፡
ዛሬ ደግሞ ይህ አይን ያወጣ ሆኖ መጥቷል፡፡ ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ እንደዘገበው ሁሉም የኬንያ በእረፍት ላይ ያሉም ሆኑ ስራ የለቀቁ ፖሊሶች በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ወደአገሪቱ እንዳይስፋፋ ለመከላከል በሚል ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር ጄኔራል ኤድዋርድ ምቡጉዋ ለሁሉም የፖሊስ ጣቢያዎች በላኩት መልእክት ፖሊሶቹ እስከሰኞ ወደስራቸው ተመልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉ ትእዛዝ መስጠታቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
ይህንን ትእዛዝ የሰጡት የኬንያ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው፡፡ በፕሬዝደንት ኬንያታ የሚመራው ምክር ቤቱ ሁሉም የፀጥታ አካላት ንቁ እንዲሆኑና ሀይላቸውን እንዲያደራጁ መወሰኑን ጋዜጣው ጠቅሷል፡፡ በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለውና ስምንት መቶ ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ድንበር ላይም የጥበቃው ቁጥጥር እንዲጠናከር ትእዛዝ ያስተላለፈው ምክር ቤቱ ይህ በተለይም የህገ ወጥ ስደተኞችንና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያን ዝውውር ለመከላከል እንደሚረዳ መግለፁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት በሃገራቸው ይህን ሲያደርጉ ከርመው ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።