ስኮትላንዳዊው አንትሮፖሎጂስት ማይክል ክራውሊ በኢትዮጵያ አትሌቶች ላይ ጥናት አድርጓል

(ዘ-ሐበሻ ዜና) ስኮትላንዳዊው አንትሮፖሎጂስት ማይክል ክራውሊ እ.ኤ.አ በ2015 ወደኢትዮጵያ በመሄድ ለአስራ አምስት ወራት ኖሯል፡፡ በእነዚህ ወራት ዋነኛ ስራው የኢትዮጵያን ባህልና ከባቢ አየር ማጥናት ቢሆንም ከዚሁ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ አትሌቶች ላይ ጥናት አድርጓል፡፡

ጥናቱ ደግሞ ከርቀት ሳይሆን አብሯቸው በመኖር፣ በመሮጥና በመዋልም ጭምር ነበር፡፡ የጥናት ውጤቱንም ‹‹አውት ኦፍ ቲን ኤይር›› የሚል አዲስ መፅሀፍ በማሳተም ይፋ አድርጎታል፡፡ በመፅሀፉም የኢትዮጵያዊያንን አትሌቶች በተለይ የርቀት ውድድር ሯጮችን ስኬት ሚስጥር እንዳገኘ አስታውቋል፡፡

ሚስጥሩን ለማወቅም ሰሞኑን ለገበያ የቀረበው ይህ መፅሀፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸበቸበ ይገኛል፡፡ መፅሀፉን አስመልክቶም ደራሲ ከበርካታ ሚዲያዎች ጋር ቃለ መጠይቅ እየተደረገለት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ከፖዲየም ራነር ጋር ያደረገው ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ቃለምልልስ ‹‹የኢትዮጵያና የምስራቅ አፍሪካ የረጅም ርቀት ሯጮችን ስኬት ለማጥናት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡ አንተ ባደረከው ጥናት ምን አገኘህ?›› ተብሎ ተጠይቆ ነበር፡፡

ክራውሊ ሲመልስ ‹‹ከኢትዮጵያ ሯጮች ጋር በቆየሁበት ወቅት አንድ የተገነዘብኩት ነገር እነሱ በታለንት አያምኑም፡፡ የሚያምኑት በትክክለኛው ቦታ አስፈላጊውን ልምምድ ማድረግ ለውጤት ያበቃል በሚል ነው፡፡ ስለዚህም ያለመታከትና ያለመሰልቸት ስለሚለማመዱ ለውጤት ይበቃሉ›› ሲል ተናግሯል፡፡