የተከበበው የሕወሃት ትርፍራፊ ጦር የገባበትን ቀለበት ሰብሮ ለመውጣት ከፍተኛ ውጊያ መክፈቱ ተሰማ

(ዘ-ሐበሻ ዜና) በቆላ ተንቤን ከደረሰብት ከባድ እልቂት አምልጦ የወጣውን የሕወሓት ኃይል ለመያዝ የሚደረገው ኦፕሬሽን እንደቀጠለ መሆኑን የዘ-ሐበሻ የመከላከያ ምንጭ ገለጹ። እንደምንጩ ገለጻ በአራት ቀን ውጊያ ቆላ ተንቤን ያለው የሕወሓት አመራሮችን የሚጠበቀው ትርፍራፊ ኃይል ሲደመሰሰ በዚያው ተሸሽገው የነበሩት አመራሮች አምልጠቅ “ባቲሽ” ወደተባለች መልክአ ምድሩ እጅግ አስቸጋሪ ወደ ሆነ ቦታ አምልጠዋል።

Crisis in Ethiopia Map

በዚህ አስቸጋሪ ስፍራ ውስጥ ወደ የትም አቅጣጫ ለማለፍ ቀለበት ውስጥ የገቡት የሕወሓት አመራሮች ወደየትም ማለፍ እንዳይችሉ ተከበው ቆይተዋል። ከቦ መቆየት ያስፈልገውም የተደበቁበት መንደር መልክአ ምድሩ በአየር ካልታገዘ ብዙ መስዋእትነት ሊያስከፍል ስለሚችል ያህንን ለመቀነስ በሚል ነው ያሉት ምንጩ፤ አሁን ላይ የተደበቀው ኃይል ምግብን ጨምሮ ሎጂስቲክ እያገኘ ባለመሆኑ የገባበትን ቀለበት ሰብሮ ለመውጣት ከፍተኛ ውጊያ መክፈቱን ነግረውናል።

የተራረፈው የሕወሓት ኃይል ሰብሮ በመውጣት ከዚህ አካባቢም ለመሸሽ እያደረገ ባለው ውጊያ የአካባቢው መልከአ ምድርን ለመከላከልና በደፈጣ ለማጥቃት እየተጠቀመበት እንደሚገኝ የሚናገሩት ምንጩ ለ እንደዚህ ያለው ውጊያ አመቺው የአየር ድጋፍ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም የአካባቢው ማህበረሰብም በዚህ መንደር የደበቃቸውን የሕወሃት አመራሮች አሳልፎ እንዲሰጥ የማግባባት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች በተለይ ሰላማዊ ሰዎች ወደ ቀለበቱ እንዳይገቡ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል። ሰላማዊ ሰዎች ቢሞቱ ግድ የማይላቸው የሕወሓት አመራሮች ሆን ብለው መልክአ ምድሩ ያልተመችና ሰላማዊ ሰዎችን ለጉዳት በሚያጋልጥ ቦታ ሆነው ውጊያ እንደሚከፍቱ ምንጩ አልሸሸጉም።